" የመኪናው አንዱ የፊት ጎማ ከነቸርኬው ወልቆበት ፊት ለፊት ይጓዝ ከነበረ ሲኖትራክ ጋር በመጋጨቱ ነው አደጋው የደረሰው " - የኦሮሚያ ክልል ትራፊክ ደህንነትና ቁጥጥር ዋና መምሪያ ➡️ በሁለት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል ! የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከድር ፤ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ  ከሞጆ ወደ ባቱ ይጓዙበት የነበረው ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪ ባጋጠመው የግጭት አደጋ ህይወታቸው አልፏል። ቃላቸውን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ትራፊክ ደህንነትና ቁጥጥር ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር  በላቸው ቲኪ ፥ በፈጣን መንገድ ከሞጆ ወደ ባቱ ይጓዝ የነበረ ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪ ከሲኖ ጋር በመጋጨቱ የአንድ ሰው ህይወት ወዲያው ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል። አደጋው የደረሰው ከቀኑ 9፡20 ሲሆን ኮድ3-75541 ኢት ላንድክሩዘር መኪና  አንዱ የፊት ጎማ ከነቸርኬው ወልቆበት ፊት ለፊት ይጓዝ ከነበረ ሲኖትራክ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። በወቅቱ ምንም ዓይነት ግጭት ሳይኖር የፊት ጎማው የወለቀበት ምክንያት እየተጣራ መሆኑን ለቴሌቪዥን ጣቢያው አመልክተዋል። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ፥ በአቶ አሊ ከድር ድንገተኛ ህልፈተ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ፤ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ከተካሄደ የአመራሮች ስብስባ ወደ ስራ ሲመለሱ አደጋው እንዳጋጠመ ጠቁመዋል። @tikvahethiopia